ዳንጎቴ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ከባድ
የኤሌክትሪክ የጭነት መኪና አስመረቀ
ዳንጎቴ ሲኖትራክ የተሰኘው ጥምር ኩባንያ፣ በናይጄሪያ ሌጎስ በሚገኘው ፋብሪካው በሀገር ውስጥ የተገጣጠመ የመጀመሪያውን ከባድ የኤሌክትሪክ የጭነት መኪና በይፋ አስመረቀ። የዳንጎቴ ግሩፕ፣ የሲኖትራክ እና የሌጎስ ግዛት አመራሮች በተገኙበት በዚህ መድረክ ላይ፣ የሲኖትራክ ፕሬዝዳንት ሊዩ ዌይ ተሽከርካሪው በመላው አፍሪካ በሀገር ውስጥ የተገጣጠመ የመጀመሪያው ዘመናዊ የኤሌክትሪክ የጭነት መኪና መሆኑን ተናግረዋል።
ይፋ ከሆኑት ተሽከርካሪዎች መካከል ዋነኛው በአንድ ጊዜ ቻርጅ እስከ 200 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችል ሲሆን፣ በፍጥነት ቻርጅ የሚያደርግ ዘመናዊ መሳሪያም አብሮ ቀርቧል። ከዚህም በተጨማሪ እስከ 350 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችል ሌላ ትልቅ የኤሌክትሪክ ተሳቢ መኪና መዘጋጀቱ ተገልጿል። ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ከ8,000 በላይ የናፍጣና የጋዝ መኪኖችን ሲገጣጥም የቆየው ይህ ኩባንያ፣ አሁን ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቴክኖሎጂ ፊቱን አዙሯል።
የዳንጎቴ ግሩፕ ከፍተኛ ኃላፊ ዴቫኩማር ኤድዊን እንደገለጹት፣ ይህ እርምጃ የአካባቢ ብክለትን ከመከላከል ባለፈ የነዳጅና የስራ ማስኬጃ ወጪን በእጅጉ የሚቀንስ የወደፊቱ የትራንስፖርት አቅጣጫ ነው። የሌጎስ ግዛት ባለስልጣናትም ተሽከርካሪዎችን ከውጭ ከማስገባት ይልቅ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ የተወሰደ ትልቅ እርምጃ መሆኑን በመግለጽ አድናቆታቸውን ቸረዋል።
#afromekina
Loading content...
