" የነዳጅ አቅራቢ ተቋሙ ባለፉት ስድስት እና ሰባት ወራት ውስጥ ብቻ ወደ 480 ቢሊየን ብር ተጨማሪ ዕዳ ተሸክሟል " -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)
👉 " በተወሰነ ደረጃ ዋጋን ወደ ሕዝብ ማውረድ ካልተቻለ በአንድ ሊትር 90 ብር እየደጎምን ማስቀጠል እንቸገራለን "
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው ግጭት ምክንያት በተፈጠረ የውጭ የዋጋ ግሽበት (Imported inflation) ሳቢያ ወደ ነጠላ አሃዝ ወርዶ የነበረው የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት መልሶ ወደ 14.7 በመቶ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ እንደገለጹት፣ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ድረስ ወደ ነጠላ አሃዝ ገብቶ የነበረው የዋጋ ንረት የኢራኑን ግጭት ተከትሎ በዓለም ገበያ ላይ በተፈጠረው የሸቀጦች ዋጋ መጨመር ምክንያት መልሶ ከፍ ብሏል።
በዚህም ምክንያት በዓለም ገበያ ላይ ነዳጅ በሊትር እስከ 90 ብር ገደማ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወደብ የሌላት ኢትዮጵያ ግን በምስራቅ አፍሪካ ካሉ ሀገራት በእጅጉ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ነዳጅ እያቀረበች መሆኗን በንጽጽር አስረድተዋል።
በምስራቅ አፍሪካ አንድ ሊትር ነዳጅ በኬንያ 1.7 ዶላር፣ በጅቡቲ 1.77 ዶላር፣ በዩጋንዳ 1.57 ዶላር፣ በታንዛኒያ 1.53 ዶላር እንዲሁም በሩዋንዳ 2 ዶላር ገደማ እየተሸጠ ባለበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ የመንግስት ተመን 1.04 ዶላር ብቻ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ይህንን ዝቅተኛ ዋጋ ለማስቀጠል መንግስት ባደረገው ድጎማ ምክንያት የነዳጅ አቅራቢ ተቋሙ ባለፉት ስድስት እና ሰባት ወራት ውስጥ ብቻ ወደ 480 ቢሊየን ብር ተጨማሪ ዕዳ መሸከሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ድጎማው ቀጣይነት ሲያብራሩ "ማስቀጠል ይቻላል ወይ ለተባለው በዚያ መንገድ ማስቀጠል አይቻልም በተወሰነ ደረጃ ዋጋን ወደ ሕዝብ ማውረድ ካልተቻለ በአንድ ሊትር 90 ብር እየደጎምን ማስቀጠል እንቸገራለን"ብለዋል።
በነዳጅ ድጎማ አሰጣጥ ላይ ድጎማ የሚገባቸውንና የማይገባቸውን አካላት የመለየት ሥርዓት ባለመኖሩ ኩባንያዎችና የውጭ ኢምባሲዎች ጭምር የድጎማው ተጠቃሚ መሆናቸው ተገቢ እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ረገድ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ አመልክተዋል።
ከሎጂስቲክስና ከመርከቦች ዝውውር መስተጓጎል ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ኪሳራ እና የኮንትሮባንድ ሥጋት ለመቅረፍም መንግስት ከዳንጎቴ ኩባንያ ጋር በጋራ በመሆን ከጅቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ የሚዘረጋ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ (Pipeline) እና የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ግንባታ መጀመሩን አስታውቀዋል።
"ይሄ ችግር ያስተማረን ትምህርት እና ኢንቨስት ማድረግ የግድ ያስፈልጋል የሚል አንድ ጥሩ ትምህርት (Lesson) ያገኘንበት ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ መርከቦች ወደብ ላይ በመቆየታቸው የሚከፈለውን ተጨማሪ ወጪ (Demurrage) በእጅጉ እንደሚቀንስ ገልጸዋል።
#afromekina
Loading content...
